Wednesday, July 17, 2013

የተክለሀይማኖት አስተዳደርና ምዕመናን እየተወዛገቡ ነው


(Addis Admass :- ) የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ጊዜያዊ የልማት ግንባታ፤ በአስተዳደሩ፣ በምዕመናኑና በሠንበት /ቤቱ መካከል ውዝግብ አስነሳ፡፡ ቤተክርስቲያኑ በዋናው አስፋልት መንገድ በኩል 12-20 የሚደርስ ህንፃ ሰርቶ እንዲጠቀም ቢፈቀድለትም ዋናውን ግንባታ ለመጀመር አቅሙ ስለማይፈቅድ ጊዜያዊ ገቢ ማስገኛ ሱቆች ተሠርተው ቤተክርስቲያኑ እንዲጠቀም የተወሠነው ውሳኔ ለውዝግቡ መነሻ እንደሆነ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ጊዜያዊ ልማቱን ቤተክርስቲያኑ ባለው በጀት ሠርቶ መጠቀም እየቻለ፣ በደብሩ አስተዳደርና ዋና ፀሀፊ የውስጥ ለውስጥ ድርድር ለአንድ ባለሃብት መሠጠቱን በመቃወማችን ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰብን ነው ብለዋል - ምዕመናንና የሰንበት /ቤት ተወካዮች፡፡የደብሩ አስተዳደርና ዋና ፀሀፊው ከባለ ሀብቱ ጋር በመደራደር አንድ ትልቅ መጋዘንና 10 ሱቆችን ለራሱ፣ ሌሎች 10 ሱቆችን ለቤተክርስቲያኑ ሠርቶ ሊያስረክብ እንዲሁም ለራሱ የሠራውን 10 ዓመታት በነፃ ሊጠቀም መዋዋላቸው አግባብ አይደለምሲሉ ምዕመናንና የሰንበት /ቤት ተወካዮች ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡

ጊዜያዊ ልማቱን ግለሠብ ይስራው ከተባለም ጨረታ ወጥቶና በግልፅ ተፎካክሮ እንጂ ቤተክርስቲያኑ የሚመራበት ሠበካ ጉባኤ ሳይወስን በግለሠቦች ድርድር ሊሆን እንደማይገባ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡ አሁን ከስራቸው በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁት የሠበካ ጉባኤው አባላት፤ በመጀመሪያ ጉዳዩ ተድበስብሶ ስለቀረበላቸው አምነውበት እንደነበር፣ ነገር ግን የተቃዋሚው ምዕመናንና የሠንበት /ቤቱ ተወካዮች ቁጥር እየበዛ በመሄዱ ጉዳዩን እንደገና በመመርመር አካሄዱ ችግር እንዳለው በተደጋጋሚ ለደብሩ አስተዳደር ማስረዳታቸውን በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው አስፍረዋል፡፡የደብሩ ዋና ፀሀፊ ሊቀ ህሩያን ሲሳይ /ማሪያም በበኩላቸው፤ ጉዳዩ ውስጥ ለውስጥ የተካሄደ ነው መባሉ ሀሰት መሆኑን ጠቁመው፤ ጉዳዩን ተስማምተው ከፈረሙት ዘጠኝ የቤተክርስቲያኒቱ የሠንበት /ቤት ተወካዮች፣ ምዕመናንና የአስተዳደር አካላት ውስጥ አሁን ስራ የለቀቁት የሠበካ ጉባኤ አባላት ፊርማ ያለበትን ቃለ ጉባኤ በማቅረብ ጉዳዩ ታምኖበትና ሥምምነት ላይ ተደርሶ የተፈፀመ ነው ብለዋል፡፡
 
ዋና ፀሀፊው አክለውም፤ ቃለ ጉባኤው ሲፈረም ከማህበረ ካህናት አራት ሠዎች፣ ከምዕመናን ሶስት፣ የደብሩ አስተዳዳሪና ዋና ፀሀፊው በድምሩ ዘጠኝ ሠዎች የተስማሙበት እንደሆነ ተናግረዋል። ቤተክርስቲያኑ ባለው ገንዘብ ጊዜያዊ ልማቱን ማሠራት ይችላል መባሉንና ያለ ጨረታ ለምን ለግለሠብ ግንባታው እንደተሠጠ ጠይቀናቸው ዋና ፀሀፊው ሲመልሱ፤በግል ጥቅም ምክንያት ለግለሠብ ሠጡ የተባለውን እቃወማለሁ፤ ጨረታን በተመለከተም ባዶ መሬት ላይ መጥታችሁ እንዲህ አድርጉ ይህን ስሩ ማለት አንችልም። ምክንያቱም መሬት የመንግስት ነውብለዋል፡፡ በመሆኑም ጉባኤው በተሠጠው ስልጣን መሠረት የተፈቀደውን ህንፃ እስክንጀምር ድረስ ጊዜያዊ ሱቆች ለማሰራት ተወስኗል ብለዋል፡፡ ዋና ፀሀፊው ይህን ይበሉ እንጂ ቅሬታ አቅራቢዎች ጉዳዩ አስጊ ሁኔታ ላይ በመሆኑ ጉዳዩን ለምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፅህፈት ቤት ያቀረቡት ሲሆን /ቤቱም ለደብረ አሚን ተክለሀይማኖት /ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ /ቤት በፃፈው ደብዳቤ፣ የልማት ስራው እስኪጣራ ድረስ ሁሉም እንቅስቃሴ እንዲቆምና ከስራ የለቀቁት የሰበካ ጉባኤው አባላት ወደ ስራ እንዲመለሱ አዟል፡፡
 
በቤ/ክርስቲያኑ ውስጥ ሙስና እንደሚፈፀም የገለፁት ምዕመናኑ፤ለክ/ከተማ እና ለማዘጋጃ ቤት ማግባቢያ የሚውል 50ሺህ ብር ያለ ደረሠኝ እንዲወጣ ትዕዛዝ የተላለፈበት ደብዳቤ እንዳለ ጠቅሰው ይሄም በደብሩ የተንሰራፋው ሙስናና ብልሹ አሠራር ያሳያልብለዋል፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ጉባኤ ኤርሚያስ /ኢየሱስን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ባይሳካም የደብሩ ዋና ፀሐፊ ሊቀህሩያን ሲሳይ፤ ገንዘቡ የወጣበት ደብዳቤ በደብሩ አስተዳዳሪ ያልተፃፈና በሰዎች ተጭበርብረው የፈረሙት መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዩ በፖሊስ ምርመራ እየደረገበት እንደሆነ ገልፀዋል። ምዕመናኑ በበኩላቸው፤ ጉዳዩ ለምዕራብ አበባ ሀገረ ስብከት /ቤት ቀርቦና ተረጋግጦ የሀገረ ስብከት /ቤቱ ገንዘቡ የወጣው ከህግና ደንብ ውጭ በመሆኑ፣ በአስቸኳይ ወደ ባንክ እንዲገባ ለደብሩ አስተዳደር በደብዳቤ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

1 comment:

  1. ቅዱስ ሃብት በላቸውJuly 28, 2013 at 11:47 AM

    “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት” ዮሐ.2፥16
    እጅግ ግራ ከሚገቡኝ ነገሮች አንዱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየቤተክርስቲያኑ አፀድ ስር እየተሰሩ ያሉት የንግድ ሱቆች ነገር ነው። በዚህ በኩል የቤተክርስቲያናችን መተዳደሪያ ሕግ ምን እንደሚል የማውቀው ነገር የለም። ነገር ግን አሁን በስደት በምኖርበት አገርም ሆነ ካሁን ቀደም በነበርኩበት ግብፅ ውስጥ ያሉ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንዲህ አይነቱን ነገር ፈጽሞ አላየሁም። የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት ከሚሸጥባቸው አነስተኛ ሱቆች በስተቀር፣ የሚገኘው ትርፍ ተሰልቶ ሌሎች የንግድ ማዕከሎች ከቤተክርስቲያን ሕንፃ ጋር ተጎራብተው በመገንባት ስራ ላይ የዋለባቸው አብያተ-ክርስቲያናት ማየቴን አላስታውስም።
    በርግጥ ይህ መሰሉ ነገር በአገራችን የሚደረገው "አድባራቱ በቂ ገቢ ስለሌላቸው ነው" የሚል ምክኒያት ሊቀርብ ይችላል። ነገር ግን ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው እግዚአብሔርን ሊያመሰግንና ሊያመልክ የሚሻ ምዕመን ከፈጣሪው ጋር እንዲገናኝባት እንጅ ሻጭና ገዥ እንዲገናኝባት አይደለምና በበኩሌ ይህ ነገር ሊዋጥልኝ አልቻለም። ደግሞም አሁን ባለሱቅ እየሆኑ ያሉት የአዲስ አበባ ደብሮች የገቢ ችግር የሌለባቸው መሆናቸውን ልብ ይሏል። ደግሞም ዓላማው ገቢ ለማስገኘት ከሆነ ከቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውጭ የሆነ ስፍራ ተመርቶ የታለመውን መተግበር አይቻልም ወይ?
    ባብዛኛው እነዚህን ሱቆች ለመገንባት የሚውለው ቦታ ደግሞ ካሁን ቀደም መካነ መቃብር የነበረ በመሆኑ የሰው ልጆችን አፅም በግሬደር እየዛቁ ሌላ ቦታ ወስዶ መድፋት የግድ ነው የሚሆነው። በዚህ በኩል በአዲስ አበባዋ የማህደረ-ስብሓት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ዛሬ ቆሞ የሚታየው ኮሌጅና ሱቅ በሚገነባበት ወቅት ያየሁትን መግለጽ እሻለሁ። በወቅቱ አሁን ሕንፃው ያረፈበትን መሬት ለማስተካከል በግሬደር የተዛቀውን አፈር ያለልክ የጫኑ ገልባጭ መኪኖች ከቤተክርስቲያኑ ርቆ የልደታ ፀበል በላይ ያለ ሜዳ ላይ (የድሮው አይሮፕላን ማረፊያ አጠገብ) ለመድፋት ሲከንፉ፣ በርካታ የሰው ልጆች ቅሪተ-አካል ከቤተክርስቲያኑ እስከዚህ ስፍራ ያለው መንገድ ላይ እንደአልባሌ ነገር ወድቆ ይታይ እንደነበር አስታውሳለሁ። እንዲያውም ዛሬ እያነሳሁት ያለው ጥያቄ ለመጀመሪያ ጊዜ በውስጤ ያጫረው ያኔ ነበር ማለት እችላለሁ።
    ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበዓለ ሆሳዕና በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ የሚከተለው ሕዝብ ሁሉ “ ሆሳዕና በአርያም ” እያሉ እያመሰገኑትና እየሰገዱለት ቤተ መቅደስ ደረሱ፡፡ በዚያን ጊዜ ግን የአይሁድ ካህናት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የተለያዩ እንስሳትንና አእዋፍን ሲሸጡና ሲገዙ ነበር። እስኪ መጽሃፍ ቅዱሳችን ይህንኑ አስመልክቶ የሚጠቅሰውን ላካፍላችሁ “ በመቅደስም በሬዎችንና በበጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፤የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፤ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ ርግብ ሻጪዎችንም ‘ይህን ከዚህ ውሰዱ ፤የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት’ አላቸው፡፡” ዮሐ.2፥14-16
    ይህ ብቻም አይደለም። ቤተ ክርስቲያን የፀሎት ስፍራ እንደሆነች በግልጽ የተቀመጠባቸው በርካታ ጥቅሶችን ከመፅሃፍ ቅዱሳችን መምዘዝ ይቻላል። ለምሳሌ፦
    “ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ” ”(ማር.11፥17)
    “ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል” (ሉቃ.19፥45)
    “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች " (ማቴ.21፥13 )
    በዚህ በኩል አሁን እየተሰራ ያለውን ነገር ከመፅሃፍ ቅዱስ ቃልና ከቤተክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ ጋር እያስማማ የሚተነትኑልንን ሊቃውንት አነጋግራችሁ ብታቀርቡልን መልካም ነው ስል በዚህ አጋጣሚ መልዕክቴን ላስተላልፍላችሁ እወዳለሁ።
    ቅዱስ ሃብት በላቸው
    (አውስትራሊያ)

    ReplyDelete